የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለ2 ቀን ሲያካሂድ የነበረው የአካዳሚክ ዘርፍ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቀቀ

በመማር ማስተማር ሂደት አንገብጋቢ የሚሆኑትን የግብአት እጥረት በመለየት እየተፈታ እንደሚሄድ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጋርዳቸው ወርቁ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ሐምሌ 15 እና16 /2016 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ 7 ኮሌጆችና አንድ የህግ ትምህርት ቤት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ ያካሄዱ ሲሆን፣ በየኮሌጁ ጠንካራ አፈጻጸም የታየባቸው ስኬቶች ተወስተዋል።

ኮሌጆች ከበጀት ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን የግብአት እጥረት ያነሱትን አስመልክቶ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ(ዶ/ር ) የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት አስቸጋሪ እንደነበር ገልፀው፣ ኮሌጆቹ በተለይም ለትምህርት መርሐ-ግብር ማስፋፋት የሚጠይቁትን ሙሉ በሙሉ ማሟላት ባይቻልም አንገብጋቢ የሆኑትን በመለየት ለ2017 ዓ.ም እንዲሟላ ይደረጋል ብለዋል።

ፕሬዘዳንቱ አያይዘውም “የተሻለ ልምድ ያካበታችሁ መምህራን ስልጠና በመስጠትና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለመማር ማስተማር ሥራው የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት የ2016 ዓ.ም የበጀት እጥረትን አስመልክቶ ከመምህራን ለተነሳው ጥያቄ ደግሞ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንት ክንዴ ብርሀን(ዶ/ር) ባለፈው በጀት ዓመት በተወሰኑ ኮሌጆች የማህበረሰብ አገልግሎት

የተቋረጠበት ምክንያት በበጀት እጥረት መሆኑን ገልፀው፣ ለቀጣይ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ለስራ ዝግጁ እንሆናለን ብለዋል፡፡

የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ሕንጻ ግንባታው ቢጠናቀቅም መሰረተ ልማት እንዲሟላለት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዘዳንት ወሀቤ ብርሃን(ዶ/ር) ገልፀዋል።

ሐምሌ16/2016 ዓ.ም