የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና(Neuro Surgery) አገልግሎት ለመሰጠት ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና (Neuro Surgery) አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጋርዳቸው ወርቁ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል የማይሰጡ አግልግሎቶችን ከእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል አስተዳደር እና ከክልል ጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት ደረጃ በደረጃ የማስጀመር እና የእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታልን ደረጃ የማሻሻል ስራ እንደሚሰራ ጨምረው ተናግረዋል።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ጥገና ስፔሻሊቲ የሆኑት ዶ/ር መስጠት ይበልጣል በኩላቸው በእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል ከዚህ በፊት ከሚሰጡ ህክምናዎች በተጨማሪ የአንጎልና ህብለ ሰረሰር ህክምና (የአዋቂወች እና ህፃናት አንጎል ድንገተኛ አደጋወች/Adult Traumatic and pediatric Brain injuries፣ የአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ/Intracranial Hematomas፣ የአዋቂወች እና ህፃናት አንጎል እጢ ህክምና/Brain Tumor surgery፣ የአንጎል ውስጥ ፈሳሽ ግፊት መጨመር/Hydrocephalus፣ የአንጎል ውስጥ ድንገተኛ የደም ፍሠት መቋረጥ ወይም መፍሠስ/Stroke) እና ተያያዥ ህክምናዎች ከዚህ በኋላ መሰጠት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡
የእንጅባራ ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዳካል ዳይሬክተር ዶ/ር አዲሱ ሙሉሰው በበኩላቸው ሆስፒታሉ ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን በስፔሻሊስት ሀኪሞች ለማህበረሰቡ የተሻለ ህክምና እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓት በሀገር ደረጃ ህክምናው በውስን ቦታዎች የሚሰጠውን የአንጎል እና ህብለ ሰረሰር ህክምና ለመስጠት ዩኒቨርሲቲው ስፔሻሊስት ሀኪም መቅጠሩን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ይህን ህክምና ለማግኘት ባህዳር እና አዲስ አበባ ለሚላኩ ታካሚዎች እንግልት እና አላስፈላጊ ወጪ የሚያስቀር በመሆኑ በቀጣይ ጥቂት ቀሪ ሥራዎችን አጠናቆ በሙሉ አቅም አገልግሎቱን ለመስጠት ሙሉ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በሰው ኃይል እና በሌሎች ዘርፎች እያደረገ ላለው ትልቅ ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ነሐሴ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ