ከተለያዩ የጤና ተቋማት ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት ተጀመረ

      ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም፤ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት ጤና ቢሮና ከአዊ ብሔረሰብ ጤና መምሪያ ጋር በመተባበር ከተለያዩ የጤና ተቋማት ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች በተግባር የታገዘ የክትባት ስልጠና (Imunization in practice) መስጠት ጀምሯል። ስልጠናው ለተከታታይ 6 ቀናት የሚቀጥል መሆኑም ተገልጿል።

የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ዳንኤል አዳነ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ክትባት የህክምና ሂደት ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን ከተላላፊ በሽታዎች ለመጠበቅ የሚያስችል በመሆኑ በሽታን የመከላከል አቅም ላይ ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ የክትባት ሽፋን(Full Immunization Coverage) 57.72 ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት ግብ ከሆነው 90% ና በላይ ጋር ሲነፃፀር ብዙ ሊሠራ እንደሚገባ አመላካች መሆኑን በማብራራት ተሳታፊ የጤና ባለሙያዎች በስልጠናው ያላቸውን ችሎታ የሚያጠነክሩበት ሰፊ ውይይቶችና የተግባር ልምምድ የሚያደርጉበት፤ እንዲሁም የቅርብ ጊዜ አሠራር መመሪያዎችን፣ ምርጥ ልምዶችና አዳዲስ ነገሮች ላይ እውቀት የሚያገኙበት በመሆኑ ስልጠናውን በትኩረት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተከታታይ ሙያ ማበልፀጊያ (CPD) አስተባባሪ መ/ርት የውብምርት ሻረው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሙያ ማበልፀጊያ (CPD) ማዕከል የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠን የሚችልበትን ሙያ ፈቃድ ሐምሌ07/2015 ዓ.ም እንደወሰደ ጠቅሰው የስልጠናው ዓላማ በሥራ ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ከወቅቱ አዳዲስ አሰራሮች አኳያ ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱና እንዲያሳድጉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።