እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጋር የጋራ መግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

የመግባቢያ ስምነነት ሰነዱ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመሥራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑም ተገልጿል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጋርዳቸው ወርቁ(ዶ/ር) በስምምነት ፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ቱሪዝም እና ሥራ ፈጠራ በሀገር ደረጃም ትኩረት የተስጠው ዘርፍ ከመሆኑም ባሻገር የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲም አንዱ የትኩረት መስክ መሆኑን በመጥቀስ በአካባቢው ያለውን እምቅ ያልተነካ የቱሪዝም ሀብት ለመጠቀም ልምድ ካለው ተቋም ጋር መስራት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ተቋማቱ በተናጠል ያላቸውን ልምድ፣ ዕውቀትና ክህሎት አቀናጅቶ በመጠቀም ሀገራዊ ፕሮጀክቶችንና ኮንፈረንሶች በማዘጋጀት ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ሆቴል ዘርፍ ዕድገት አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚቻልም ተናግረዋል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው በእንጅባራ አካባቢ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራን በማከናወን የቴክኖሎጅ ሽግግር በማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸው ተቋማቸው ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት በመፈራረሙ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሁለቱ ተቋማት በኩል የጋራ የጥናትና ምርምር ሥራዎችንና ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ በጋራ ማከናወን፣
የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ለሠራተኞች እና ለተማሪዎች ልምድ ልውውጦችን ማድረግ እንዲሁም
በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ማኅበረሰባዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ተግባራዊ ማድረግ የስምምነቱ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸው ተገልጿል።

ነሃሴ -07-2014 ዓ.ም

እንጅባራ ዩንቨርሲቲ፤