እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በ2016 ዓ፣ም  ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት አበረከተ

ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና  ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል፡፡

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጋርዳቸው ወርቁ(ዶ/ር) በሽልማት ፕሮግራሙ ላይ እንደገለጹት በብሄረሰብ አስተዳደሩ በ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተናን በችግር ውስጥ ሆነው ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ  ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ጋርዳቸው አያይዘውም ሽልማቱ እና እውቅናው በቀጣይ ህይወታቸው ከዚህ የተሻለ እንዲሰሩ የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸው እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለብሄረሰብ አስተዳደሩ የተለያዩ ድጋፎች ሲሠጥ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
ዶ/ር ጋርዳቸው አክለውም  በዩኒቨርሲቲው 59 የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች ህክምናን(Medicine) ጨምሮ እንዲሁም 47 የ2ኛ ዲግሪ(1ፒ.ኤ.ች ዲግሪ) ፕሮግራሞች መኖራቸውን ገልጸው እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ባሉት ፕሮግራሞች ብዛት እና ጥራት ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወዳዳሪ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወንድማገኝ ማኔ እንደገለጹት እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በብሄረሰብ አስተዳደሩ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረው በዛሬው ዕለት በተዘጋጀው የሽልማት እና ዕውቅና መርሃ ግብር መደሰታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር  ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሽልማት የተበረከተላቸው 9 ተማሪዎች ሲሆኑ  ከአገው ምድር አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ሀና ፈቃዱ 548፣ዮሴፍ መርከቡ  520፣መክበብ ታየ 519፣ቢኒያም ጥሩነህ 514፣ ማሪያማዊት መንበሩ 513 እና  ሀና አይናለም 476 ፣ከአንከሻ  ወረዳ ፈለቀ ቸኮል  512፣ ከቻግኒ ከተማ አስተዳደር እመቤት ወርቅነህ 505 እንዲሁም ከጥሪጊ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት  ደርበው አይችሉም 505 በማምጣት ዩኒቨርሲቲው ለእያንዳንዳቸው 10ሽህ ብር በድምሩ የ90 ሽህ ብር  ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡
ሽልማት ከተበረከተላቸው ተማሪዎች  መካከል  ተማሪ እመቤት ወርቅነህ እንደተናገረችው በሽልማቱ መደሰቷን ገልጻ  በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ  በመመደቧም በጣም ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡
በሽልማት መርሃ ግብሩ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንቶች፣የተማሪ ወላጆች እና የዩኒቨርሲቲው ሌሎች መካከለኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን ሽልማት የተበረከተላቸው ተማሪዎች እና ወላጆችም ዩኒቨርሲቲው ለሠጣቸው ሽልማት አመስግነዋል፡፡
በመጨረሻም ተሸላሚ ተማሪዎች እና ወላጆች የዩኒቨርሲቲውን ግቢ ጎብኝተዋል፡፡
ጥቅምት 27/2017ዓ.ም፤

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ