በእንጅባራ ዩኒቪርሲቲ የእንሰሳት እርባታ ማዕከል የልምድ ልውውጥ ተካሄደ

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የውጭ ዝርያ ያላቸውን የወተት ላሞች በመግዛት ማርባት የጀመረ ሲሆን በማዕከሉ የሚመረተውን ወተት በተመጣጣኝ ዋጋ በዋናነት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እያቀረበ ይገኛል፡፡
ማዕከሉ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ዘዴን በመጠቀም የወተት ከብቶችን እያረባ እንደመሆኑ መጠን በአካባቢው በወተት ልማት ላይ ለተሰማሩ የእንስሳት አርቢዎች ተሞክሮውን የማካፈል ሥራ ተከናውኗል፡፡

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ክንዴ ብርሃን (ዶ/ር) እንደተናገሩት የእንስሳት እርባታ ማዕከሉ በዋናነት የተቋቋመው የእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር እየሠሩ የሚለማመዱበት፤ተማሪዎችና መምህራን የምርምር ሥራ የሚሠሩበት፤የዝርያ ማሻሻል ስራ የሚሠራበት፤ለአካባቢው ማህበረሰብ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው እንስሳት የሚቀርቡበት፤ በዘርፉ የሚፈለጉ የማህበረሰብ አገልግሎቶች ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰጡበት እና የዩኒቨርሲቲው የውስጥ ገቢ የሚገኝበት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ነው፡፡ ማዕከሉ እነዚህን አላማዎች ለማሳካት የሚሰራቸውን ተግባራት የአካባቢው ማህበረሰብ በማየት ልምድ መቅሰምና አሠራሩን ማዘመን ስለሚገባው በማእከሉ የተደረገው የልምድ ልውውጥ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ዶ/ር ክንዴ ተናግረዋል፡፡