በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የስንዴ ምርጥ ዘር መዝራት ተጀመረ

ዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ከግንባታ ውጭ የሆኑ ቦታዎች ላይ የተለያዩ የሰብልና የአትክልት ዘሮችን በመዝራት ላይ ሲሆን በዛሬው እለት የስንዴ ምርጥ ዘር መዝራት ተጀምሯል፡፡

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት  ክንዴ ብርሃን (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ለማህበረሰብ አገልግሎት የሚውሉ የተሻሻሉ የሰብልና የአትክልት ዝርያዎችን ለማስፋፋት በምርምር የተደገፈ የምርጥ ዘር ብዜት እንደሚያከናውን ገልጸው በዛሬው እለት የተጀመረው በስድስት ሄክታር መሬት ላይ የሚዘራው  የስንዴ ምርጥ  ዘር ብዜት  የዩኒቨርሲቲውን የውስጥ ገቢ ከማሳደግ በተጨማሪ የተሻለ ምርት የሚያስገኝ የስንዴ ዘር ለአርሶአደሩ ለማሰራጨት እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ምግብና አየር ንብረት እጽዋት ሳይንስ ኮሌጅ የአግሮኖሚ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት  አማረ አለምነው(ዶ/ር) በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ለጊዜው አገልግሎት የማይሰጠውን መሬት አገልግሎት ላይ አውለን ለግው ገቢ ማስገኘትና ለአርሶአደሩ የተሻሻለ ምርጥ ዘር ስንዴን ማሰራጨትን አላማ አድርገን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡አያይዘውም ዘጠኝ ኩንታል ደንዳ (c1) የተባለ ምርጥ የስንዴ ዘር እየዘሩ መሆናቸውን እና በቀጣይም የተለያዩ ሰብሎችን በማፈራረቅ በስፋት ለማምረት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡

ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም፤

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ