ለ “STEM” ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑ ተገለጸ

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ ሦስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ እና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በ2ኛ ዙር የክረምት መርሐ ግብር እየተማሩ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ክንዴ ብርሃን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ በሳይንስ ትምህርቶች ላይ የተሻለ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች በክረምት እና በበጋ የሳምንቱ እረፍት ቀናት ሲያስተምር የቆየ መሆኑን አስታውሰው በዚህ ዓመትም ከእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ 3ቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎችን በተግባር የተደገፈ ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ትምህርት በተግባር እንዲሰሩ በማሰብ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ፣ የኮምፒውተር እና ቨርቹዋል ላብራቶሪዎች በተጨማሪም ለተማሪዎች አስፈላጊ የምግብ እና መኝታ ቁሳቁሶች መሟላታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ፕሮግራም የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ተማሪዎች ያገኙትን ምቹ አጋጣሚ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ

ነሃሴ- 01/2016